ከነገስታት እስከ ጃንጥራር...... ከአፄ ይኩኑ አምላክ እስከ ጃንጥራ አስፋው......ባጠቃላይ ምድሩ የነገስታትና የንጉስሳውያን ምድር ነው ይህ ብቻ አይደለም ወድህ የአራት አይናወቹ የነ ሸህ ሰይድ ጫሌ(ረህመቱላህ አለይህ😍) መፈጠሪያ ምድር! ወድህ ደሞ የግማደ መስቀሉ መገኛ ግሸን ደብረ ከርቤ መገኛ ምድር😍 ሌላም አለ... ከአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች አምባሰል ቅኝት የተገኘውም በዚሁ ድንቅ ምድር አምባሰል ነው! ሌላም ብዙ ብዙ ይባልለታል አምባሰል!
ትዝታ.... አምባሰል.... ባቲ.... አንችሆየ ቅኝቶች መገኛቸው ወሎ❤ ነው!
አምባሰል ወረዳ...
አምባሰል ተንዶ ግሸን ደግፎታል፤
አምባሰል መናዱ ያንቺ ቃል ፈርሶ ነው፤
ግሸን መደገፉ የኔ ቃል ማክበር ነው፤
ይብላኝልሽ ላንቺ ቃልሽ ለፈረሰው፤
የጁን መች ያጠዋል ቆሞ ከሄደ ሰው።
የተባለለት አምባሰል ወረዳ በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች አንዱ ሲሆን ስሙ በወረዳው ውስጥ ከሚገኝ አምባ ስም ይመነጫል።
አምባሰል ወረዳ፣ በደቡብ ምዕራብ የባሽሎ ወንዝ ከጠንታ ወረዳ ሲለየው፣ በደቡብ የባሽሎ ገባሪ የሆነው ወላኖ ወንዝ ከኩታበር፣ እንዲሁ የ ሚሌ ወንዝ ደግሞ በስተ ደቡብ ምስራቅ ከ ተሁለደረ ወረዳ ይለየዋል። 44% የሚሆነው የወረዳው ክፍል ተራራማ፣ 36% ወጣ ገባ፣ 12% ገደላማ ሲሆን 7.5% ብቻ ለጥ ያለ ሜዳ ነው። ስለሆነም በዚህ ወረዳ አራት አይነት የአየር ንብረቶች ይገኛሉ።
እነዚህም ውርጭ ፣ ደጋ ፣ ወይና ደጋ እና ቆላ ሲሆኑ እያንዳንዳቸው 47%፣ 29.53%፣ 49.64%፣ 20.36% ይይዛሉ። የዚህ ወረዳ ታላቁ ከተማ ውጫሌ ሲሆን በአካባቢው በሚገኝ የተፈጥሮ ከሰል ክምችት ይታወቃል።
የኢጣሊያ ወራሪ ሃይል ይህን የከሰል ክምችት አገር እስከለቀቀበት ዘመን ድረስ ይጠቀም ነበር።
የዓፄ ይኩኖ አምላክ እናት ከሰገረት እንደመጣች ሲነገር፣ አባቱ ደግሞ ከዚህ ቦታ እንደመነጨ ይጠቀሳል። በዚህ ምክንያት ይመስላል፣ የዚህ አምባ ባለስልጣኖች ጃንጥራር በሚል ልዩ ማዕረግ ከጥንት ጀምሮ እስከ ንጉሳዊው ስርዓት ፍጻሜ አካባቢውን ያስተዳድሩ ነበር (ከቅርብ ምሳሌ እቴጌ መነን የጃንጥራር አስፋው ልጅ ነበሩ)።
የይኩኖ አምላክ የልጅልጅ የሆኑት ዓፄ ጅን አሰገድ ተገዳዳሪ የነገሥታት ወንድ ልጆችን በዚህ ወረዳ በሚገኘው አምባ ግሸን ላይ ማሳሰር እንደጀመሩ ታሪክ ጸሐፊው ዋሊስ ባጅ ይጠቅሳል። እኒህ የሚታሰሩት ሰዎች ቤተ እስራኤል ወይንም በቀላሉ እስራኤላውያን ይባሉ ነበር። ስለሆነም ከአምባ ግሸን አጠገብ የሚገኘው ተራራ አምባ እስራኤል ወይንም አምባ ሰል መባል ጀመረ።
በ1682 ዓ.ም. የታተመው የ ቪቼንዞ ኮሮኔሊ ካርታ አምባ ሰልን በአምኅራ ግዛት የሚገኝ ተራራ እና የንጉሳዊ ቤተሰቦች መያዣ እንደሆነ ያሳያል ። ቆይቶ የጣሊያን ወራሪዎች ከመምጣታቸው በፊት አምባሰል ከተራራ ስምነት ባሻገር የአስተዳደር ክፍል ስም በመሆን ከዋና ከተማው ማርየ ስላሴ ይተዳደር ነበር።
በጣሊያን ወረራ ጊዜ የአምባሰል ዋና ከተማ ጎልቦ ሆነ፣ ለዚህም ምክንያቱ ለ አዲስ አበባ - መቀሌ መንገድ ጎልቦ ስለሚቀርብ ነበር። ጣሊያኖች ሲባረሩ ዋና ከተማው ውጫሌ ተብሎ በወረዳነቱ ጸና። ቀጥሎ የአውርጃ ስርዓት ሲተገበር አምባሰል፣ ተሁለደረ እና ወረ ባቦ አንድ ላይ ሆነው የአምባሰል አውራጃን መሰረቱ። የአውራጃው ዋና ከተማ ሐይቅ ነበር።
የደርግ ስርዓት በአውራጃነቱ ካስቀጠለው በኋላ የዞን ስርዓትን ሲተገብር አውራጃውን ወደ መሰረቱት ወረዳዎች በመክፍል አምባሰል በወረዳነቱ ጸና። በዚህም በአሁኑ ወቅትም 23 ቀበሌዎችን አቅፎ ይገኛል።
ወሎ ደሴ